የበገና መዝሙር ዲ/ን አቤል ተስፋዬ ላንዴ እስከወዲያኛዉ ግጥም መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ቴዎድሮስ በለጠ ዜማ ዲ/ን ዘላለም ታከለ (ዘጎላ)
🍁 ላንዴ እስከወዲያኛው
ያንን ሰው ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም ሴት በሆንኩ
ላልወጣ ገብቼ ፡ ላልመለስ በሔድኩ
~~~~~~~~~~~~~~~
ምነው እሱን በሆንኩ
ያን የቀኝ ወንበዴ
ብመስለው ላ’ንድቀን : ባየው መንገዴ
ለመስረቅ አይደለም ንብረት ለመቀማት
አልያም ለመዝረፍ ሕይወትን ለማጥፋት
በዚያ መንገድማ
ከሱስ ብበልጥ እንጂ መች ከእርሱ አንስና
እኔን ታውቀኝ የለ …
የወንበዴ አለቃ ያ’ጢኣተኞች ዋና
ያ … ጸጸት ያዘለ
በዚያች የጭንቅ ሠዓት «አስበኝ» እያለ
ከመስቀልህ ጥላ ከሥር ስለዋለ
ካ’ዳም ቀድሞ ገባ ምሕረት ተቀበለ
እኔም እንደ ጥጦስ : ማታዬ እንዲያምር
ብትለኝ ምን አለ? …
«ከገነት ተጠለል: ዛሬን ከእኔ እደር»
🍁 ላንዴ እስከወዲያኛው
ያንን ሰው ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም ሴት በሆንኩ
ላልወጣ ገብቼ ፡ ላልመለስ በሔድኩ : ዛሬን ከእኔ እደር»
ደ’ሞ ይህን ተመኘሁ
ለንጊኖስን በሆንኩ
ያቺን ዕለተ ዓርብ : ቀራንዮ በዋልኩ
ለአመጽ አይደለም : ከከአይሁድ ለማበር
አልያም ለመውጋት : ያንተን ጎን በጦር
በዚያ መንገድማ
አንተን ለማሳመም: ማን እኔን መሰለ
ስንቴ እንዳቆሰልኩህ …
ስንቴ እንደወጋሁህ : እኔን ታወቀኝ የለ!
ያ …የጲላጦስ ጭፍራ
በመስቀል ላይ ሳለህ በሞት በመከራ
በጦሩ ቢወጋህ ሳያዝን ሳይራራ
ከቀኝ ጎን አፍስሰህ ውኃው ከደም ጋራ
በፍቅርህ ስታስረው ዐይኑን ስታበራ
ትዕግስትህን ጎትቶት ባንተ እንደ ተጠራ
ምናለ እንደው ’ኔንም …
ላንተ ብቻ እንዲያድር : ልቤን ብታበራ
🍁 ላንዴ እስከወዲያኛው
ያንን ሰው ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም ሴት በሆንኩ
ላልወጣ ገብቼ ፡ ላልመለስ በሔድኩ ሰው ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም
ምነው በመሰልኳት
የቺን አመንዝራ
እንደርሷ ላንድ ቀን : ከፊትህ ብጠራ
ለዝሙት አይደለም ነፍሴን ለማሳደፍ
አልያም ለመርከስ መቅደስክን ለማጉደፍ
በዚያ መንገድማ
ነውርን በመሸከም : መች ከእርሷ አንሳለሁ
ሕግህን በማፍረስ …
እኔን ታውቀኝ የለ : ምን እነግርሃለው
ያቺን … ድኩም ዘማ
በኃጢአቷ ቆስላ በበደሏ ታ’ማ
ዓለም ተሰብስቦ ሕይወቷን ሊቀማ
እንዲወግሯት ሳትፈርድ ቸርነትህ ቀድማ
መሬቱን ስትጭር ድምጽህ ሳይሰማ
ነውሯን እንደቀበርክ በከሳሽ ፊት ቆማ
ዳግም አትበድዪ : በፍቅር ሂጂ እንዳልካት
እንደው የኔንም ነፍስ …
ምናለ መልሰህ: እንዲያ በማረካት
🍁 ላንዴ እስከወዲያኛው
ያንን ሰው ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም ሴት በሆንኩ
ላልወጣ ገብቼ ፡ ላልመለስ በሔድኩ ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም ሴት
✍️๏ በአግናጥዮስ 🖊 ሕዳር ካህናተ ሰማይ ፳፻፲፫ ዓ.ም ተፃፈ
☞ ከምድር ጌጥ ታላቋ ደብረ ሊባኖስ