MENU

Fun & Interesting

አባ መቃርስ - ክፍል - 1 / Aba Mekars Part - 1 Ye Kidusan Tarik

Video Not Working? Fix It Now

ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ወይም ቅዱስ መቃሬ 'ጽድቅ እንደ መቃርስ' የተባለለት: የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም ወይም አስቄጥስን የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው:: በ4ኛው መቶ ክ ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሳቸው አጥምቀዋል:: በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጠራሩ ይክበርና እመቤታችንን: ቅዱሳን ሐዋርያትን: አዕላፍ መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን: ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: ማርቆስን: ዼጥሮስን: ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል:: ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከ2 ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል:: ስለ ታላቁ ቅዱስ መቃርዮስ ቅድስና ለመጻፍ መነሳት በረከቱ ብዙ ነው:: ግን 'ዓባይን በጭልፋ' እንዲሉ አበው ከብዛቱ የተነሳ የሚዘለቅ አይሆንም:: ቅዱስ መቃርስ ከዘመናት በላይ በቆየበት የበርሃ ሕይወቱ:- 1.አባ ብሶይ: አባ ባይሞይ: አባ ሳሙኤል: አባ በብኑዳን ጨምሮ እርሱን የመሰሉ ወይም ያከሉ ቅዱሳንን ወልዷል:: 2.ለሕይወታችን መንገድ የሚሆኑንን ብዙ ቃላትን ተናግሯል:: 3.ከገዳማት እየወጣ በብዙ ቦታዎች ቅዱስ ወንጌልን ሰብኩዋል:: 4.አጋንንትን ድል ከመንሳት አልፎ እንደ ባሪያ ገዝቷቸዋል:: 5.ለዓይንና ጀሮ ድንቅ የሆኑ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶችም ቤተ ክርስቲያን "ርዕሰ መነኮሳት ወይም የመነኮሳት ሁሉ አለቃ" ስትል ትጠራዋለች:: በ97 ዓመቱ መጋቢት 27 ቀን ሲያርፍ መላእክት ብቻ ሳይሆን አጋንንትም ስለ ድል አድራጊነቱ ዘምረውለታል:: ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ ወይም የሳስዊር ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት: ወላጆቹ ወይም አብርሃምና ሣራ ይባላሉ የኖሩባት ቦታ ናት:: የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው:: በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት ወይም በረከትን ሲሹ አደረጉት:: ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለ160 ዓመታት ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ-ዘመን ግን ተንባላት ወይም እስላሞች መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት:: በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ:: ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን" ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው:: መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው:: በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ:: ሕዝቡም በዝማሬና በማሕኅሌት: ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ:: ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል:: አምላከ ቅዱሳን የታላቁ ቅዱስ መቃርስን ትሕትናውን: ትእግስቱንና ቅንነቱን ያድለን:: በበረከቱም ይባርከን:: ምንጭ ››› " ዝክረ ቅዱሳን Saints Of The Orthodox Church " የፌስቡክ ገፅ - https://www.facebook.com/%E1%8B%9D%E1%8A%AD%E1%88%A8-%E1%89%85%E1%8B%B1%E1%88%B3%E1%8A%95-Saints-Of-The-Orthodox-Church-1394454374194081/?hc_ref=ARRiQv0AKqHkvOSRqWU5HF8lVIteONOtQXQMMNRgFWIIdBKJKWgZcpuN1rvTuWMWskY&fref=nf ይህን መንፈሳዊ ፊልም አዘጋጅተውና ተርጉመው ላቀረቡልን ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

Comment