የእመቤታችን ስደት yemebetachn sedetLow,480x360, Webm
ከሰማይም ሆነ ከምድር በታች እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓይነት ፍጡር የለም፡፡
የሰው ፍጥረት አይተካከላትም፡፡
ምድራዊ ውበትን ከሰማያዊ ውበት ጋር አንድ ያደረገች ፍጹመ- ፍጽምት ናት፡፡
እንደእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓይነት የሚጣፍ ስም ከሚጣፍጥ ማንነት ጋር የተገኘ እስከዘላለሙ የለም፡፡አይወለድም፡፡
እግዚአብሄር ከፍጥረት በፊት ያከበረውና ያስቀደመው ቢኖር እንኳን እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ እንደሆነች ቅዱሳን መጽሀፍትን አንብቦ መረዳት በቂ ይመስለኛል፡፡
ለማመን የሚዳግተው ካለም እግዚአብሄር ይግለጥለት እላለሁ
በእግዚአብሄር መለኮታዊ አእምሮ ውስጥ ከፍጥረት በፊት ቀድማ የተገኘች ወይም ቀድማ የታሰበች ስም ብትኖር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአምላክ ልቦና ውስጥ ታስባ ትኖር ነበር ስንል ሰዎች ያቀዱት ነገር ልክ ጊዜው ሲደርስ ሀሳባቸው እውን እንደሚሆን አስተሳሰብ ዓይነት አይደለም ፡፡
በአምላክ መለኮታዊ ልቦና ውስጥ በማይታይ ረቂቅ ሚስጥሩ ተስላ ተቀምጣለች እንጂ፡፡
ሰው ሀሳቡን ሊረሳ እቅዱን ሊሰርዝ እና ሊተወው ወይም በሌላ በተሻለ ሊለውጠውና ሊቀይረው ይችላል፡፡
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአምላክ ልቦና ውስጥ ታስቦ መኖር ልዩ የሚያደርገው አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፡፡
በአምላክ ልቦና ውስጥ ለዘላለም ከፍጥረት በፊት ታስቦ መኖር የታየበት ወይም ሚስጥሩ የተገለጠበት ይህ ድንቅ ስራ የስላሴ ብቻ ነው፡፡ከዚህ መነሻነት በዚህ መለኮታዊ ሚስጥርና መለኮታዊ ድንቅ አስተሳሰብና ስራ ላይ የሚለወጥ ወይም የሚሻሻል ምንም ነገር እንደሌለ ልናምን ይገባናል፡፡
ስለእመቤታችን ዘላለማዊነት ወይም ከፍጥረት በፊት እንደነበረች በርካታ ምክንያቶችን ከቅዱሳት መጽሀፍት ማንሳት ይቻለን ይሆናል፡፡
ዋናው ቁምነገር ማጣቀሻ ቃላቶችን እና አንቀጾችን እያነሱ የክርክር መድረኮችን መዘርጋት ሳይሆን ልብ ያለው ሰው ካለ ልብ ይበል ድንግልን ከመጽሀፍ ቅዱስና ሌሎች የቤተክርስቲያን መንፈሳውያን መጽሀፍት ከሚያስረዱት እና ከሚናገሩት ቃላት በላይ በአምላክ ልቦና ውስጥ ተጽፋ የኖረች ዘላለማዊ እናት መሆኗን ሳይጠራጡ ማመን ከምንም በላይ ዕድለኝነትና መመረጥ ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ ታላላቅ አንባቢዎች እና መጽሀፍ ቅዱስን ተርጓሚዎች ስለእመቤታችን ዘላለማዊ እናት መሆኗን ለመመስከር በሚል ለመከራከሪያ ወይም ለማሳመኛ የሚሆኑ የአንቀጽ ቁጥሮችን ከየምዕራፍና ገጾች ውስጥ በጥልቀት ሲፈለፍሉ ይታያሉ፡፡
ቢሆንም እንዲሁ ይደክማሉ፡፡ግን ይህ እግዚአብሄር የሚወደው ዓይነት የዕውቀት መዳረሻ ወይም ሰውን ማሳመኛ መንገድ አይደለም፡፡ ይልቁንም ትውልዱ ሁሉ በእምነት እንዲጓዝ ከማድረግ ይልቅ ምዕራፍና ቁጥር ናፋቂ እና አፍቃሪ ሁኖ እንዲቀር አድርጎታል፡፡
መጽሀፍ ቅዱስን ማመን ማለት አካላዊ ቃል የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማመን ማለት ነው፡፡
ይህን ከተረዳን መጽሀፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩት እያንዳንዱ ቃላቶች ስለእግዚአብሄር አምላክነት ወይም ስለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት የሚመሰክሩ ናቸው፡
በፍቅር ተሸንፎ የሰውን ስጋ የተዋሀደው ቃል ደግሞ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነ እሳተ መለኮት ነው፡፡
ከዚህ ሚስጢር የምንረዳው ነገር ቢኖር እያንዳንዱ የመጽሀፍ ቅዱስ ቃል በአንቀጽና በምዕራፍ የተከደነና የተሸፈነ መሆኑ ነው፡፡
በመሆኑም በመጽሀፍ ቅዱስ የተጻፈውን እያንዳንዱን ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰልን እያንዳንዱ ቃላትን ያሰሩ ምዕራፍና አንቀጾች ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡
ለዚህ ነው እኮ ታዲያ አንድም እመቤታችንን አንቀጸ ብርኀን ብለው በፍቅር የሚጠሯት፡፡ ስለዚህ ከመጽሀፍ ቅዱስ ከሚገኙት አንቀጾች ውስጥ ስለእመቤታችን የሚናገር ቃል ኖረም አልኖረም እርሷ የመጽሀፍ ቅዱስ ምዕራፍና አንቀጽ ነች፡፡ ለምን ቃል፣ሆሄ ፣ዓረፍተ ነገር ያለምዕራፍና አንቀጽ ህይወት አልባ ነውና፡፡
ስለዚህም ለሰው ልጅ መዳን እመቤታችን መኖር አለባት ለጌታም መወለድ እመቤታችን መኖር ነበረባት ዓለም ያለእመቤታችን አይድንም የተባለው በዚህ ምክንያት ነው የእናቴ ልጅ፡፡